Friday, June 12, 2015

ወበዛቲ ዕለት ሰኔ 5

አእምሩ ከመ ተሰብሐ እግዚአብሔር በጻድቁ =>ዘፍ19:3 
እግዚአብሐር በጻድቁ እንደተገለጠ እወቁ =>መዝሙረ ዳዊት 4:3 ++++እንኳን ለጻድቁ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን የጻድቁ አባታችን አቡነገብረ መንፈስ ቅዱስ ፀሎት ,ምልጃና እረድሂት በረከታቸው በሁላችን ላይ ይደርብን አሜን !!!!!!!!
ፃድቁ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስዝክረ ጻድቅ ለዓለም ይሄሉ (የጸድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል።) መዝ.111፡6ቅድመ ዓለም ዘሀሎ አለም ከመፈጠሩ በፊት ለነበረ ለእግዚአብሔር አብ እና የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን ለለበሰ ለእግዚአብሔር ወልድ እንዲሁም ከእነሱ ባለመራቅ ለሚኖር ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል፡፡ ስለ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በማብዛት አይደለም በማሳነስ በማስረዘም አይደለም በማሳጠር እንድጽፍ ያነሳሳኝ እግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ጌትነትና ውዳሴ ይገባዋል አሜን በእውነት፡፡“እግዚአብሔር ያፈቅሮሙ ለጻድቃን እግዚአብሔር የዐቅቦሙ ለፈላስያን፡፡“ (እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፡፡)“” መዝ.፻፵፭፡፰ (145፡ 8)አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሀጋራቸው ንሂሳ ግብጽ ነው፡፡ አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ፡ ይባላሉ፡፡ ልጅ አጥተው 30 ዘመን ሲያዝኑ ኖረዋል፡፡ አንድ ቀን አቅሌሲያ ቤተ እግዚአብሔር ገብታ ከሥዕለ ሥላሴ ሥር ወድቃ ስትማጸን ክብሩ ከሰማይ ከፍታ የሚበጥ ልጅ እንኪ ተቀበይ የሚል ድምጽ ሰማች፡፡ በዚሁ መሰረት አባታችን መጋቢት 29 ተጸንሰው ታህሳስ 29 ተወለዱ፡፡ ዓይን በገለጹ ጊዜ ከሚታይ ነገር ላይ እንዲያርፍ እርሳቸውም በተወለዱ ጊዜ አፈፍ ተነስተው “ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ዘአውጻእከኒ እምጽ ልመት ውስተ ብረሃን” ብለው በማመስገናቸው ኋላም ምድራዊ መብል መጠጥ ሳይመገቡ ሳይጠጡ ለምስጋና ተግተው በመኖራቸው መላዕክትን ይመስላሉ፡፡ሦስት ዓመት ሲሆናቸው ቅዱስ ገብርኤል ከእመቤታችንና በገነት ካሉ ቅዱሳን ዘንድ አስባርኮ ገዳማውያን ካሉበት ምኔት ወስዶ ከበሩ አኖራቸው፡፡ አባ ዘመደ ብርሃን አሳድጎ አስተምሮ ከመዓርገ ምንኩስና አድርሷቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ “ሀብተ ፈውስ” ተሰቷቸዋል፡፡ በአንድ ቀን እልፍ እውራንንና አንካሳን ፈውሷል፡፡ ኋላ ግን ኤጲስ ቆጶሳቱ ካህናቱ ዝናቸውን ሰምተው እየመቱ ግብር የሚያስፈቷቸው ቢሆን ቅዱስ ገብርኤል በክንፉ ነጥቆ ከጌታ ፊት አቀረባቸው፡፡ በገድልህ በትሩፋትህ ከሞተ ነፍስ ከርደተ ገሃነም የሚድኑ ብዙ ነፍሳት አሉና ከሰው ተለይተህ ወደ ጫካ ግባ፡፡ ኑሮህም ከ60 አናብስተና ከ60 አናምርት ጋር ይሁን አላቸው፡፡ ጌታዬ ምን ተመግበው ይኖራሉ? ብለው ጌታን ጠየቁት፡፡ “ዘኬድከ ጸበለ-እገሪከ ይልህሱ ወበውእቱ ይጸግቡ…” የረገጥከውን ትቢያ ልሰው ያው ምግብ ሆኗቸው ይኖራሉ፡፡ ብሏቸው ውሳጤ ገዳም ገብተው ከአናብስትና አናምርት ጋር ይኖሩ ጀመር፡፡ ዳንኤል በአናብስት ጉድጓድ በጣለ ጊዜ አናብርቱ እንደ ድመት ከእግሩ በታች ሆነው እንደተገኙ የረገጡትን ትቢያ ይልሱ ይታዘዟቸውም ነበር፡፡ በዚህ መልኩ መልአኩ 30 ዓመት ከቆዩ በኋላ ጌታ ባንድነት በሦስትነት ተገልጾ “ምን ላድርግልህ ትሻለህ?” አላቸው፡፡ መጀመሪያ ላሉበት መጸለይ ይገባልና የምድረ ጋቦታን ሰዎች ማርልኝ አሉት፡፡ 3000 ሃጥአንን ከሲኦል አውጥቶ ገነት አግብቶላቸዋል፡፡ “ሑር ምድረ ኢትዮጵያ ወበህየኒ ሀላውከ ነፍሳት ዘታወጽኦሙ ወደ ኢትዮጵያ ሂድ” አላቸው፡፡ ቅዱስ ገብርኤል በሰረገላ ነፋስ ጭኖ ምድረ ከብድ አድርሷቸዋል፡፡ ዳግመኛም ወደ ዝቋላ ደብር ቅዱስ ወስዷቸው ከዚያ ሆነው በንጽሐ ልቦና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሃጢአት አይተው ከባሕሩ በራሳቸው ቆመው ይጸልዩ ጀመር፡፡ አርባ ቀን ሲሆናቸው መልአኩ መጥቶ “ዘገብረ ተዝካረከ ወዘጸውዐ ስመከእምሕር ለከ ብሎሀል” አላቸው፡፡ መላ ኢትዮጵያን ካልማረልኝ አልወጣም ብለው መቶ አመት ሲጸልዩ ኑረዋል፡፡ ከመቶ አመት በዃላ ጌታ “ተንስእ ወጻእ መሐርኩ ለከ ኩሎ ኢትዮጵያ ምሬለሃለሁ ውጣ” ብሏቸው ወጥተዋል፡፡ከዚህ በኋላ ምድረ ከብድ ወርደው ከምድር በላይ ከሰማይ በታች ሆነው ሰባት ዓመት እንደ ትኩል አምድ ሆነው ዓይናቸውን ሳይከድኑ ሰባት ዓመት ቆመው ጸልየዋል፡፡ ሰይጣንም በምቀኝነት ተነሳስቶ ቁራን መስሎ መጥቶ አይናቸውን አንቁሮ አሳወራቸው፡፡ ሁለት ሱባኤ ሲፈጽሙ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል መጥተው እፍ ብሏቸው አድነዋቸዋል፡፡ ከዚያ ተነስተው ወደ ዝቋላ ሲሄዱ ሥላሴን በአምሳለ አረጋውያን ከጥላ ስር አርፈው አገኟቸው፡፡ በእግዚአብሔር ዙፋን ተማጽነናል አዝለህ አንድ አንድ ምዕራፍ ሸኘን አሏቸው፡፡ አዝለው ከሸኙአቸው በኋላ በአንድነት በሦስትነት ሆኖ ታያቸው ደንግጠው ወደቁ፡፡ አንስተው ዝቋላ ወርደህ ጠላቶችህን ተበቀላቸው አሏቸው፡፡ በዘባነ መብረቅ ደርሰው ሰባቱን ሊቃነ መላእክት አጋዥ አርድገው እልፍ አዕላፍ አጋንንትን በማጭድ አጭደዋል፡፡ እንዲህ ለሰሚዕ እፁብ በሆነ ግብር ዓመት በኢትዮጵያ 262 ኖረው በ562 ዓመታቸው በተስፋቸው ያመነውን በኪዳናቸው የተማጸነ ጌታ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ሊምርላቸው ተስፋቸውን ተቀብለው በዕለት በዕለተ እሁድ ዐርፈዋል፡፡መላእክት በአክናፈ እሳት ኢየሩሳሌም ወስደው በየማነ ምስዋዕ ቀብረዋቸዋል፡፡ሮሜ 12፡12፣ 15፡30፣ያዕ5፡ 16፣ መዝ.88፡3፣111፡6 ምሳ.10፡7 ማቴ10፡ 40-42ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በቅዱስ ላሊበላ ዘመነ መንግስት መሆኑ ስለሚታወቅ ከ9- 14ኛው ም/ዓ ድ/ል/ክ መሆኑ ነው፡፡ ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኝ፣ ካለማወቅ ወደ መረዳት ያደረሰኝ አነሳስቶ ላስጀመረኝ አስጀምሮ ላስፈጸመኝ ጥንት ላሌለው ቀዳማዊ ፍጻሜ ላሌለው ድህራዊ ያልኖረበት ጊዜ የሌለ የማይኖርበት ጊዜም የማይኖር የዘላለም ንጉስ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን በራስ ፀጉሬ ቁትር በአጥንቶቼም ልክ አመሰግናለሁ፡፡በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡
ምንጭ፡- መዝገበ ታሪክ፣ ነገረ ቅዱሳን፣ የወርሃ ጥቅምት ስንክሳርና ገድላቸው፡፡

ወበዛቲ ዕለት ሰኔ 5
እንኳን ለኃያሉ ሰማዕት ቅዱስ ብሶይ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣አደረሰን።
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
ቅዱስ አባ ብሶይ ሰማዕት
ቅዱሱ አባታችን ከዘመነ ሰማዕታት ጣፋጭ ፍሬዎች አንዱና ግንባር ቀደሙ ነው:: ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ማጠናቀቂያ አካባቢ ‪#‎ታግሕስጦስና_ክሪስ‬ የሚባሉ ክርስቲያኖች ነበሩ:: በቀናው የጽድቅ ጐዳና ቢኖሩም ከጋብቻ በሁዋላ ለ17 ዓመታት መውለድ አልቻሉም::
የ17 ዓመት ልመናቸውን የተመለከተ እግዚአብሔር ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ አበሰራቸው:: "ሕጻኑ ለሰማዕትነት ተመርጧልና ብሶይ በሉት" አላቸው:: ብሶይ በተወለደ በ7 ዓመቱ ወላጆቹ ይማር ብለው ወደ ገዳም ወሰዱት:: በገዳም ውስጥ መጻሕፍትን አጥንቶ ዲቁናን ተሾመ:: ወደ ዓለም ተመለስ ቢሉትም እንቢ አለ::
ከባልንጀራው ቅዱስ ዼጥሮስ ጋር ለ21 ዓመታት በድንግልና: በተጋድሎ: ጾምና ጸሎትን እያዘወተሩ ኖሩ:: ቅዱስ ብሶይ 28 ዓመት በሞላው ጊዜ መልዐኩ የተናገረው የትንቢት ዘመን ደረሰ:: በርካታ ምዕመናን ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ ታረዱ:: ወደ እሳትም ተጣሉ:: ሞትን የፈሩ ደግሞ በየዱር ገደሉ ተሰደዱ::
ቅዱስ ብሶይም በሚያውቁት ሰዎች ተከሶ ለፍርድ ቀረበ:: ድንገት ከሰማይ ፍጡነ ረድኤት ወሊቀ መላዕክት ቅዱስ ገብርኤል ደረሰለት:: "አይዞሕ! እኔ እስከ መጨረሻው ካንተ ጋር ነኝ" አለው::
የጦር መኮንኑ ክርስቶስን እንዲክድ አባበለው:: ቅዱሱ ግን ጣዖታቱ የአጋንንት ማደሪያ መሆናቸውን በገሃድ ነገረው:: መኮንኑ ቢበሳጭ ወታደሮቹ እንዲጨምቁት አዘዘ:: ደሙ እየወረደ ገረፉት:: በፊትና በሁዋላ ብረት አድርገው ሥጋውን ጨፍልቀው እሥር ቤት ውስጥ ጣሉት:: ሊቀ መላዕክት መጥቶ ዳስሶ አዳነው::
መኮንኑ እርሱን ማሰቃየት ደከመው:: ‪#‎የቅዱሳን_ሕይወት‬ ግርም ይላል:: ተገራፊው እያለ ገራፊው: ስቃዩን የሚቀበለው እያለ አሰቃዩ ይደክመዋል:: ይሕንን ነው አባ ጽጌ ድንግል:-
"እመዐዛ ጽጌኪ ድንግል ውስተ ዐውደ ስምዕ ዘሰክረ:
ውግረተ አዕባንኒ ይመስሎ ሐሰረ:
እሳትኒ ማየ ባሕር ቆሪረ" ያለው::
       ቅዱስ ብሶይን ካንዱ መኮንን ወደ ሌላው እያመላለሱ አሰቃዩት:: አካሉን ቆራረጡ-ዐይኑን በጋለ ብረት አወጡ-በምጣድ ቆሉት-በጋን ውስጥ ቀቀሉት:: እርሱ ግን በፈጣሪው ፍቅር የጸና ነውና ሁሉን ታገሰ:: በነዚሕ ሁሉ የስቃይ ዓመታት ቁራሽ ዳቦ እንኩዋ አላቀመሱትም:: በረሃብ ቀጡት እንጂ:: ለርሱ ግን ምግቡ የክርስቶስ ስም ነበር::
በመጨረሻ ንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ አንገቱን በሰይፍ አስመታው:: ሥጋውንና የተቆረጠ አንገቱን ገንቦ (ጋን) ውስጥ ከቶ ጣለው:: የቅዱሱን አካል የያዘችው ጋን ግን በእግዚአብሔር ቸርነት: ማንም ሳይሸከማት ከመሬት ከፍ አለች:: ለ20 ቀናት ተጉዛ ከሶርያ ግብጽ (ቦሃ) ደረሰች:: ክርስቲያኖች ተቀብለው ሲከፍቷት የቅዱስ ብሶይ ራሱና አንገቱ ተጣብቆ ተገኝቷል:: በክብርም አሳርፈውታል::
አምላከ ቅዱሳን ከሰማዕቱ ቅዱስ ብሶይ በረከት ያሳትፈን:: በምልጃውም ይቅር ይበለን::
ሰኔ 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት፡-
1.ቅዱስ አባ ብሶይ (ኃያል ሰማዕት)
2.ቅድስት ማርታ ለባሲተ ክርስቶስ (በቅድስናዋ የተወደሰች: በስደት ያረፈች እናት ናት)
3.ቅዱስ ያዕቆብ ምሥራቃዊ
4.ቅዱስ ቢፋሞን ሰማዕት